የአቶ አንዱዓለም አራጌ ደህንነት አደጋ ላይ ነው! ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
በአሁኑ ጊዜ አቶ አንዱዓለም አራጌ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ ይገኛል፡፡ ከአስተማማኝ ምንጮች በተገኘ መረጃ መሠረት የካቲት 7 ቀን 2ዐዐ4 ዓም ከቀኑ 8፡ዐዐ ሰዓት ገደማ ለህይወቱ የሚያሰጋ ከባድ ድብደባ ተፈጽሞበታል፡፡ ድብደባውን የፈፀመው አቶ አንዱዓለም በታሰረበት ክፍል ውስጥ የሚገኝ ኢባስ አስፋው የሚባል ፍርደኛ ነው፡፡ ይህ ሰው አቶ አንዱዓለም በክፍሉ ውስጥ የግል ጉዳዩን በማከናወን ላይ በነበረበት ጊዜ በአልታወቀ ምክንያት መጀመሪያ በእርግጫ መትቶ ከጣለው በኋላ በወደቀበት ላይም አሁንም ጫማ በአደረገ እግሩ በስሚንቶ ወለሉ ላይ ደጋግሞ በመርገጥ ነፍሱን እስከመሳት የሚያደርስ ድብደባ እንደፈፀመበት ተገልፆልናል፡፡ ህይወቱ የተረፈውም በክፍሉ ውስጥ በነበሩ ታራሚዎች ገላጋይነት መሆኑም ታውቋል፡፡
ድብደባውን የፈፀመው ግለሰብ ቀደም ሲል በነፍስ ግድያ ወንጀል ተከስሶ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት የነበረ ሲሆን በኋላ ግን ይኸው ፍርድ ተሻሽሎ ቅጣቱ ወደ እድሜ ልክ እስራት የተለወጠለት እንደሆነና በማረሚያ ቤቱ ሌሎች ክፍሎች ውስጥ ለረጅም ዓመታት ታስሮ እንደነበር፤ እነ አቶ አንዱዓለም ወደ አሉበት ክፍል የመጣውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ለምን ከነበረበት ቦታ ተዛውሮ እንደመጣ ግን አልታወቀም፡፡
አቶ አንዱዓለም በተፈፀመበት ድብደባ ምክንያት ከፍተኛ የአካልና የሥነ-ልቡና ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ለህይወቱ በመሰጋት እስካሁን ድረስ ወደ ሆስፒታል ለመሔድ አልፈለገም፡፡ ምርመራና የሕክምና ርዳታ እንዲያገኝ ለማድረግ ግን በቤተሰብ በኩል ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በአቶ አንዱዓለም አራጌ ላይ የደረሰው አካላዊና ሥነ-ልቡናዊ ጉዳት ግልጽ የሚያደርጋቸው ሁኔታች አሉ፡፡ የአቶ አንዱዓለም ደህንነት አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ በሕግ ጥበቃ ሥር ያሉ ዜጎች በህይወታቸው ላይ ጉዳት እንዳይደርስባቸው የሚከላከሉ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሕጎች ቢኖሩም እየተከበሩ አይደለም፡፡
ለምሳሌ፡-
v በኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 2ዐ(3) ላይ እንደተገለፀው እስረኞች እስኪፈረድባቸው ድረስ በተከሰሱበት ወንጀል እንደጥፋተኛ የማይቆጠሩ፤ ከወንጀል ንፁህ እንደሆኑ እንደሚቆጠር ተደንግጓል፡፡ ሆኖም ‹‹በአኬልዳማ›› ድራማ በግልጽ እንደታየው መንግሥት ሙሉ በሙሉ በሚቆጣጠረው ሬዲዮና ቴሌቪዥን በወንጀለኝነት ዘመቻ አካሂዶባቸዋል፡፡
v በዚሁ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 21(1) ላይ በግልጽ እንደተደነገገው በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሠሩ ሰዎች ሰብአዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች መያዝ እንዳለባቸው ተደንግጓል፡፡ ሆኖም በአቶ አንዱዓለም ላይ የደረሰው ድብደባ ያሳየው በማረሚያ ቤት ውስጥ ሰብአዊ መብትን የሚፃረርና ለህይወት አደገኛ የሆነ ሁኔታ መኖሩን ነው፡፡
v በ1997 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ህግ አንቀጽ 110(3) ላይ ውሳኔ ያላገኙ እስረኞች ውሳኔ ከአገኙ ሌሎች እስረኞች ጋር አይቀላቀሉም በማለት በግልጽ ደንግጓዋል፡፡ እንዲሁም በኢፌድሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ተሰባስቦና ተተርጉሞ በ1998 ዓም በታተመውና ኢትዮጵያ በአፀደቀቻቸው የዓለም አቀፍ ሰነዶች በአንቀጽ 85(1) ላይ እንደተገለፀው ፍርድ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ እስረኞች እና የፍርድ ውሳኔ የተሠጣቸው እስረኞች በአንድ ክፍል አይታሠሩም በማለት በግልጽ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ሆኖም ከባድ ወንጀል ፈጽሞ ከባድ ፍርድ የተሰጠው ሰው ገና ፍርዳቸውን ከአላገኙ ሰዎች ጋር እንዲታሰር ተደርጎ በደል ተፈጽሟል፡፡
v ከላይ በተገለፀው ዓለም አቀፍ ሰነድ ውስጥ በተራ ቁጥር 84(2) ላይ በግልጽ እንደተደገገው፤ የፍርድ ውሳኔ ያልተሠጠባቸው እስረኞች ከወንጀል ድርጊት ነፃ እንደሆኑ እንደሚገመቱ ከመደንገጉም በተጨማሪ የሚደረግላቸውም አያያዝ በዚሁ ላይ የተመሠረተ መሆን እንደሚገባው ይገልፃል፡፡ ይህ ድንጋጌ አልተከበረም፡፡
በዚሁ ዓለም አቀፍ ሰነዶች አንቀጽ 67(ሀ) ላይ የእስረኞችን አመዳደብ ሲገልጽ ታሪኮቻቸው በወንጀል ድርጊቶች የተሞሉና መጥፎ ጠባይ ያላቸው እስረኞች ሌሎች እስረኞችን በመጥፎ ጠባያቸው እንዳይበክሉ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ ይህም ድንጋጌ ተጥሷል፡፡ በአቶ አንዱዓለም ላይ ድብደባ የፈፀመው ግለሰብ ከባድ ወንጀል የፈፀመ ከመሆኑም በላይ በማረሚያ ቤት ህይወቱ ፀበኛና ችግር ፈጣሪ መሆኑ ይነገራል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በተገኘው መረጃ መሠረት በአቶ አንዱዓለም ላይ ድብደባ የፈፀመው እስረኛ ከእነ አቶ አንዱዓለም ጋር ከነበረበት ክፍል ተወስዶ 3ዐዐ ያህል ታራሚዎች ወደሚገኙበት ሌላ ቤት መዛወሩ ታወቋል፡፡ እዚህ ላይ የተከሰተው አዲስና አሳሳቢ ጉዳይ ይህ ፍርደኛ በዚሁ ቤት ውስጥ ከሚገኘው የአንድነት አመራር አባል ከአቶ ናትናኤል መኮንን ጎን እንዲተኛ መደረጉ ነው፡፡ በአቶ አንዱዓለም ላይ የፈፀመውን ድርጊት በአቶ ናትናኤል ላይም ይፈጽም ይሆናል የሚል ስጋት አለን፡፡
በአቶ አንዱዓለም ላይ የተፈፀመው በደል እንዲጣራና በደል ፈፃሚው ግለሰብ ላይ ተገቢው ርምጃ እንዲወሰድ፤ ከሁሉም በላይ ግን የማረሚያ ቤቱ አስተዳደርና መንግሥት ሕገ መንግሥቱንና አግባብ ያላቸው ሕጎችን፤ እንዲሁም ሀገሪቱ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎችን በማክበር በህግ ጥበቃ ስር ላይ የሚገኙ ዜጎቻችን ህጉ በሚያዘው መሠረት ደህንነታቸው እንዲጠበቅ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) አጥብቆ ይጠይቃል፡፡
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
የካቲት 13 ቀን 2ዐዐ4 ዓም
አዲስ አበባ
—————————————————————————————–
የቢሮ ስልክ ዐ11 8 4ዐ ዐ8 11 ፖሣቁ 4222
Read in PDF : Andient Party Press Release_Feb_21_2012 (1)